በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 101

ጳውሎስ ወደ ሮም ተወሰደ

ጳውሎስ ወደ ሮም ተወሰደ

ጳውሎስ ምሥራቹን ለመስበክ ለሦስተኛ ጊዜ ያደረገው ጉዞ ኢየሩሳሌም ላይ ተደመደመ። በኢየሩሳሌም ሳለ ተይዞ እስር ቤት ገባ። ሌሊት ላይ ኢየሱስ በራእይ ተገልጦ ‘ወደ ሮም ሄደህ በዚያ ትሰብካለህ’ አለው። ጳውሎስ ከኢየሩሳሌም ወደ ቂሳርያ ተወሰደ፤ በዚያም ሁለት ዓመት ያህል በእስር ቤት ቆየ። በኋላም የአውራጃ ገዢ በሆነው በፊስጦስ ፊት ለፍርድ በቀረበበት ወቅት ጳውሎስ ‘ቄሳር ፍርድ እንዲሰጠኝ ወደ ሮም መሄድ እፈልጋለሁ’ አለ። ፊስጦስም ‘ቄሳር እንዲፈርድልኝ እፈልጋለሁ ስላልክ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ’ አለው። በመሆኑም ጳውሎስን ወደ ሮም በሚሄድ መርከብ አሳፍረው ላኩት፤ ሁለት ክርስቲያን ወንድሞቹ ማለትም ሉቃስና አርስጥሮኮስ አብረውት ሄዱ።

በባሕር ላይ ሳሉ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተነሳ። አውሎ ነፋሱ ለብዙ ቀናት ስለቆየ በመርከቡ ውስጥ የነበሩት ሰዎች በሙሉ የሚሞቱ መስሏቸው ነበር። ሆኖም ጳውሎስ እንዲህ አላቸው፦ ‘እናንተ ሰዎች፣ አንድ መልአክ በሕልም ተገልጦ እንዲህ ብሎኛል፦ “ጳውሎስ፣ አትፍራ። በሰላም ሮም ትደርሳለህ፤ አብረውህ በመርከቡ ውስጥ ያሉት ሰዎችም በሙሉ ይተርፋሉ።” ስለዚህ አይዟችሁ! ማናችንም አንሞትም።’

አውሎ ነፋሱ ለ14 ቀናት ያህል ቆየ። በመጨረሻም አሸዋማ የሆነ ደረቅ መሬት ተመለከቱ፤ ማልታ ወደምትባለው ደሴት ተቃርበው ነበር። በዚህ ጊዜ መርከቡ ከመሬት ጋር ተጋጭቶ ተሰባበረ፤ ሆኖም በመርከቡ ላይ የነበሩት 276 ሰዎች በሙሉ በሰላም ከውኃው ውስጥ ወጡ። አንዳንዶቹ እየዋኙ ሌሎቹ ደግሞ በመርከቡ ስብርባሪዎች ላይ እየተንጠላጠሉ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ደረሱ። በማልታ የሚኖሩት ሰዎችም ተንከባከቧቸው፤ እንዲሁም እንዲሞቃቸው እሳት አነደዱላቸው።

ከሦስት ወር በኋላ ወታደሮቹ ጳውሎስን በሌላ መርከብ ወደ ሮም ወሰዱት። ሮም ሲደርስ በዚያ ያሉ ወንድሞች ሊቀበሉት መጡ። ጳውሎስም እነሱን ሲያይ ይሖዋን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ። ጳውሎስ እስረኛ የነበረ ቢሆንም በተከራየው ቤት ውስጥ አንድ ወታደር እየጠበቀው እንዲኖር ተፈቅዶለት ነበር። ለሁለት ዓመት ያህል በዚያ ቆየ። ሰዎች ሊጠይቁት ይመጡ የነበረ ሲሆን ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክላቸውና ስለ ኢየሱስ ያስተምራቸው ነበር። በተጨማሪም ጳውሎስ በዚያ ሆኖ በትንሿ እስያና በይሁዳ ለሚገኙ ጉባኤዎች ደብዳቤ ጽፏል። በእርግጥም ይሖዋ ጳውሎስን በመጠቀም ምሥራቹ ለብዙ አገር ሰዎች እንዲዳረስ አድርጓል።

“በሁሉም ነገር ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን፤ ይህን የምናደርገው በብዙ ነገር በመጽናት፣ በመከራ፣ በእጦት፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች [ነው]።”—2 ቆሮንቶስ 6:4