ጥናት 19
የአድማጮችን ልብ ለመንካት መጣር
ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
-
አድማጮችህ ራሳቸውን እንዲመረምሩ እርዳቸው። አንዳንድ ጥያቄዎችን በማንሳት፣ አድማጮች ስለ ጉዳዩ ያላቸውን አመለካከት እንዲፈትሹ ለመርዳት ጥረት አድርግ።
-
በጥሩ የልብ ዝንባሌ ተነሳስተው እርምጃ እንዲወስዱ አበረታታቸው። አድማጮችህ መልካም ነገሮችን ለማድረግ የሚነሳሱበትን ምክንያት እንዲመረምሩ እርዳቸው። ጥሩ የልብ ዝንባሌ እንዲያዳብሩ አበረታታቸው፤ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ የሚያነሳሳቸው ለይሖዋ፣ ለሰዎች እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ያላቸው ፍቅር መሆን አለበት። አድማጮችህ መመሪያ እየሰጠሃቸው እንዳለ እንዲሰማቸው ከማድረግ ይልቅ የትምህርቱን ጥቅም እንዲያስተውሉ እርዳቸው። ንግግርህ የሚያበረታታና ለተግባር የሚያነሳሳ እንጂ አድማጮችህን የሚያሸማቅቅ ሊሆን አይገባም።
-
ሰዎች በይሖዋ ላይ እንዲያተኩሩ አድርግ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች፣ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ትእዛዞች የአምላክን ባሕርያት እንዲሁም ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያንጸባርቁት እንዴት እንደሆነ ጎላ አድርገህ ግለጽ። አድማጮችህ የይሖዋን አመለካከት ከግምት እንዲያስገቡና እሱን ለማስደሰት እንዲጥሩ አበረታታቸው።